ከመስከረም 16 እስከ 25 በ ኳታር አዘጋጅነት በ ዶሃ የተካሄደው 17ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሜሪካውያን የበላይነት ተጠናቁዋል።

አሜሪካ በውድድሩ 14 የወርቅ, 11 የብር እና 4 የነሃስ በድምሩ 29 ሜዳልያ በማግኘት አንደኛውን ደረጃ ስትይዝ ኬንያ በ5 ወርቅ, 2 ብር እና 4 ነሃስ በአጠቃላይ 11 ሜዳልያ ከአለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ሆናለች። ጃማይካውያን በ3 ወርቅ, 5 ብር እና 4 ነሃስ 3ኛ ሲሆኑ ቻይና በ 3 ወርቅ, 3 ብር እና 3 ነሃስ የአራተኝነትን ደረጃ አጊንታለች።

አገራችን ኢትዮጵያ በ2 ወርቅ, 5 ብር እና 1 ነሃስ ከአለም 5ኛ ከአፍሪካ 2ኛ በመሆን ውድድሩዋን አጠናቃለች። 

ከ ሁለት አመት በፊት በ ሎንደን ሞ ፋራን በ መቅደም በ 5000 ሜትር የአለም ሻምፒዮን የነበረው የ 25 አመቱ ወጣት ሙክታር እንድሪስ በ ዶሃም የ 5000 ሜትር የበላይነቱን አሳይቱዋል።
የኢትዮጵያውያን የቡድን ስራ በተደነቀበት ውድድር ሙክታር 5000 ሜትሩን በ 12 ደቂቃ ከ 58.85 ሰከንድ በመጨረስ ለአገሩ የወርቅ ሜዳልያ አስገኝቱዋል።
ሙክታርን በመከተል ሰለሞን ባረጋ የ ብር ሜዳልያ አስገኝቱዋል።

 

ለኢትዮጵያ ሌላኛውን የወርቅ ሜዳልያ የተገኘው በወንዶች ማራቶን ነው።

ገዛኸኝ አበራ በ 2001 ካመጣው ወርቅ በሁዋላ ለ 18 አመታት እርቆ የቆየውን አሸናፊነት ወደ ሃገራችን የመለሰው የ 29 አመቱ ሌሊሳ ዴሲሳ ነው።
የባለፈው አመት የ ኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ ሌሊሳ የዶሃውን ውድድር ለመጨረስ 2 ሰአት ከ10 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ ፈጅቶበታል። ከውድድሩ አንድ ሳምንት በፊት ከተካሄደው የሴቶች ማራቶን የተሻለ
የአየር ሁኔታ በታየበት ውድድር ሌሊሳን ተከትሎ ሞስነት ገረመው ሁለተኛ በመሆን ለሃገሩ የ ብር ሜዳልያ አስገኝቱዋል።

ብዙዎች በጠበቁት የ 10,000 ሜትር የወንዶች ሩጫ ኢትዮጵያ ወርቁን ብታጣም የብር ሜዳልያ በ ዮሜፍ ቀጀልቻ አማካኝነት አጊንታለች።  የ 10,000 ሜትር ውድድርን ለሁለተኛ ግዜ ብቻ የሮጠው
ዮሜፍ ውድድሩን ለመጨረስ 26 ደቂቃ ከ49 ሰከንድ ከ 34 ማይክሮ ሰከንድ ፈጅቶበታል።

በዶሃ ከተካሄዱት ውድድሮች እጅግ አስገራሚ የ አጨራረስ ፉክክር በተካሄደበት የ 3000 ሜትር  የ መሰናክል ሩጫ ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ በአንድ ማይክሮ ሰከንድ ተቀድሞ ሁለተኛ ሆንዋል።
ለሜቻ ውድድሩን 8 ደቂቃ ከ 1 ሰከንድ ከ 36 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት የ ኢትዮጵያን ሪከርድ አሻሽሉዋል።

በሴቶቹ ውድድር ከሌላው ግዜ ያነሰ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ለዚህም የ ገንዘቤ ዲባባ እና የ አልማዝ አያና በጉዳት ምክንያት ያለመሳተፍን ብዙዎች በምክንያትነት ያነሳሉ።
በ 10,000 ሜትር ለተሰንበት ግደይ በ ሲፋን ሃሰን ተቀድማ ሁለተኛ ስትሆን ውድድሩን ለመጨረስ 30 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ ከ23 ማይክሮ ሰከንድ ፈጅቶባታል ይህም የግሉዋ ምርጥ ሰአት ሆኖ ተመዝግቡዋል። በሴቶቹ ዘርፍ ሌላኛውን ሜዳልያ ለኢትዮጵያ ያስገኘችው ጉዳፍ ጸጋዬ ነች። ጉዳፍ በ 1500 ሜትር 3ኛ በመውጣት የነሃስ ሜዳልያ ስታገኝ ውድድሩን ለመጨረስ 3 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ ከ38 ማይክሮ ሰከንድ ፈጅቶባታል ይህም የግሉዋ ምርጥ ሰአት ነው።

 

በ አቤል ወንድሙ