የኢሉድ ኪፕቾጌ እና ኢባርጉየን ናሚድ አሸናፊነት
ኢሉድ ኪፕቾጌ የ34 ዓመት የረጅም ርቀት ኬንያዊ አትሌት ነዉ፡፡

ይህ አትሌት የሩጫ ህይወቱ ከፍታ ትራክ ላይ ቢጀምርም ይበልጥ በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ እንዲደነቅ የሆነው ግን ወደ ጎዳና ላይ ሩጫ ከገባ በኻላ ሲሆን በተለይም በማራቶን ሩጫ ላይ ነዉ፡፡

ኪፕቼጌ ትራክ ላይ ይሮጥ በነበረበት ወቅት በ5ሺህ ሜትር እስከ ታላቁ የዓለማችን ዉድድር ኦሎምፒክ ድርስ ተወዳድሮ ዉጤት ማስመዝገብ ችሎ ነበር፡፡

አትሌቱ በዚሁ ርቀት በዓለም አቀፍ ዉድድሮች 2 የወርቅ ሜዳልያል ለሃገሩ ኬናያ አስገኝቷል፡፡ይሁን እንጂ ኢሉድ ኪፕቾጌ ስሙ ከፍ ብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስተጋባዉ ግን በተለይ በሙሉ ማራቶን እያሥመዘገበ የመጣዉ ፈጣንና ለማመን የሚከብድ ዉጤት ነዉ፡፡

ኢሉድ ኪፕቾጌ በ2016ቱ የሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያዊዉን አትሌት ፈይሳ ሌሊሳን ቀድሞ ያገኘዉን ጨምሮ በተለያዩ ዉድድሮች አንገቱ ላይ ካጠለቃቸዉ የወርቅ ሜዳልያዎች ዉስጥ ስምንቱ በማራቶን ስፖርት ያገኛቸዉ ናቸዉ፡፡

ኬንያዊዉ አትሌት ያሳለፍነዉ የ2017/18 የዉድድር ዓመት በርካታ ድሎችን ያስመዘገበበት ዓመት ሲሆን በናይኪ ፕሮጀክት አማካይነት በልዩ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ማራቶንን ከ2 ሰዓታት በታች ለመሮጥ የተቃረበ አትሌት መባል የቻለበት ጊዜ ነበር፡፡

2:01:39 ኢሉድ ኪፕቾጌ በ2018ቱ የበርሊን ማራቶን ያስመዘገበዉ የግሉም የዓለምም ምርጡ የማራቶን ሰዓቱ ነዉ፡፡ኪፕቾጌ በዚህ እና መሰል ዉጤቶቹ ነዉ የ2018 የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ምርጡ አትሌት ለመሆን በቅቷል፡፡

ኢባርጉየን ናሚድ የ34 ኮሎምቢያዊት የስሉስ ዝላይ ተወዳዳሪ ናት፡፡ አትሌቷ በዉድድር ዓመቱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ዉድድሮች ላይ ባሳየችዉ ወጥ አቋም የዓመቷ ምርጥ እንስት አትሌት ለመሆን በቅታለች፡፡

 

ኢባርጉየን ናሚድ በመካከለኛዉ አሜሪካ፤ካሪቢያን አገራት ዉድድሮች ባሳየቺዉ ተፎካካሪነት እና በዳይመንድ ሊጉ የፍጻሜ ተፋላሚ በመሆኗም ጭምር አሸናፊ መሆኗን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድህረ ገጹ አስነብቧል፡፡