በ12ኛው የአዲስአበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ ሁለተኛው የምድብ ጨዋታ ዛሬ በምድብ አንድ ደደቢት ከ ጅማ አባ ጅፋር እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከ አዲስ አበባ ከተማ በማገናኘት ጨዋታ ተከናውኗል፡፡

ደደቢት ከ ጅማ አባ ጅፋር በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ደደቢት 12′ ደቂቃ በአንዲ ክፔኩ ብቸኛው ጎል አንድ ለምንም ማሸነፍ ችሏል፡፡

በ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ እየተጠባበቀ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር  በዚህ ውድድር ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለ ሲሆን በተለይ በዛሬ ጨዋታ ከ79 ደቂቃ በኀላ ተጭኖ በመጫወት ደደቢቶችን ማጨናነቅ ችሎ ነበር፡፡

ሁለቱም ወሳኝ የመሀል ተከላካዮቹ  ( አክሊሉ እና አይናለም ) በዝውውር  ያጣው ደደቢት የመስመር ተከላካይ እና የተከላካይ አማካይ ሚና የነበራቸው ተጫዋቾችን ወደ መሀል ተከላካይነት በማምጣት አዲስ ጥምረት በመፍጠር ላይ ያለ ይመስላል፡፡

በጨዋታው በተለይም ከዕረፍት መልስ ከተደረጉ አስደንጋጭ ሙከራዎች በደደቢት በኩል 67ኛው ደቂቃ አቤል  እንዲሁም 81ኛው ደቂቃ አክዌር ታም  ከመሀል ሜዳ የተሻገረላቸውን ኳስ ፍጥነታቸው ተጠቅመው ከጅማው በረኛ ጋር ፊትለፊት ተገናኝተው ያመከኗቸው ኳሷች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በዚህ ጨዋታ ደደቢት የመጀመርያው ሶስት ነጥብ ማግኘት የቻለ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና የተጋሯትን አንድ ነጥብ ይዘው ሶስተኛው የምድብ ጨዋታ ይጠብቃሉ፡፡

የጅማ አባ ጅፋሩ ሄኖክ አዱኛ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል፡፡

ሁለተኛው የምድብ አንድ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከ አዲስ አበባ ከተማ ያገናኘ ነበር፡፡

ጥሩ የኳስ ፍሰት እና እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጀምረው ነበር የአዲስ አበባ ከተማ ጎልን ማንኳኳት የጀመሩት በተለይ ታዳጊው አቡበከር ናስር በ6′ ደቂቃ ላይ ጎል ክልል ውስጥ ሆና ወደ ጎል ልኳት   ቋሚ ብረት የመለሰበት አጋጣሚ  አስደንጋጭ ነበረች፡፡

ወደ መሀል እና ወደ መስመር እየተመለሰ ጥሩ ቅብብሎሽን  በማድረግ የአዲስ አበባ ተከላካዮችን ሲያደናግጥ የነበረው ሳሙኤል ሳኑሜ 21′ ጎል ክልል ውስጥ በተሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቶ ወደ ጎል መቀየር ችሏል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ 38′ ላይ  50 ቁጥር ለባሹ ገናናው ረጋሳ ባስቆጠራት  አስደናቂ ጎል አቻ በመሆን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ አሁንም ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች 58′ ደቂቃ በድጋሜ ሳኑሚ ላይ በተሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣትምት አግኝተው ሳኑሚ ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ሲችል 86′ ደቂቃ ላይ አሁንም እራሱ ላይ በተሰራው ጥፋት ሶስተኛው ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቶ ወደ ጎል በመቀየር ሶስትዮሽ መስራት ችሏል፡፡

መደበኛ የጨዋታ ሰአት አልቆ 92′ ደቂቃ ላይ መሀል ሜዳ አከባቢ የተገኘው ቅጣት ምት የበረኛን መውጣትን በማየት በቀጥታ ወደ ጎል የላካትን ኳስወደ ጎብነት በመቀየር ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ወንድይፍራው ጌታሁን አስገራሚ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ቡና 4 ለ 1 ማሸነፍ ሲችል ሳሙኤል ሳኑሚየጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡