በ2017 ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ የግብፁ አል አህሊና የሞሮኮዉ ዋይዳድ ካዛብላንካ የመጀመርያ ጨዋታቸዉን ቅዳሜ 18/ 2010 ዓ/ም በግብፅ አሌክሳንድርያ፣ ቦርግ ኤል – አራብ ስታድየም ያደርጋሉ።

ሁለቱ ክለቦች በምድብ አራት ተደልድለዉ የነበሩ ክለቦች ናቸዉ። ዋይዳድ በ12 ነጥብ የምድቡ መሪ ሆኖ ሲያጠናቅቅ አል አህሊ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኝነት አጠናቋል። እርስ በርስ ባደረጉት ጨዋታ የየሜዳቸዉን ፍልሚያ በተመሳሳይ የ2 ለ 0 ዉጤት ድል ማድረግ ችለዋል።

በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ መድረክ የአል አህሊን ያህል ደጋግሞ በፍፃሜዉ ላይ የነገሰ ክለብ የለም። የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ በ1957 ዓ/ም ( እንደ አዉሮፓዉያን አቆጣጠር 1964/65 ) ከተመሠረተ አንስቶ፣ በ52 ዓመት የመድረኩ ታሪክ 10 ያህል ጊዜ ሲቀርብ በ8 ፍፃሜዎች ባለ ድል መሆን ችሏል። በ1975 ዓ/ም ( 1982 ) የመጀመርያ ዋንጫዉን መዉሰድ ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ለመጨረሻ ጊዜ ባለ ድል እስከሆነበት 2013 ድረስ በ1976 ዓ/ም እና በ2000 ዓ/ም (በ1983 እና በ2007) ብቻ ዋንጫዉን ለተቀናቃኞቹ አሳልፎ ሰጥቷል። በ2005 ዓ/ም እና በ2006 ዓ/ም በተከታታይ ዋንጫዉን ያነሳ ሲሆን፣ በተለይ ከ1998 እስከ 2001 ዓ/ም (ከ2005 – 2008) ድረስ ባሉት አራት ተከታታይ ዓመታት ለፍፃሜ የበቃ ሲሆን በአንዱ ብቻ ዋንጫዉን አጥቷል።

የሞሮኮዉ ዋይዳድ ካዛብላንካ በአንፃሩ በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ላይ የደረሰዉ ለሁለት ያህል ጊዜ፣ በ1985 ዓ/ም (1992) እና በ2004 ዓ/ም (2011) ብቻ ሲሆን፣ በ1985 ዓ/ም አልሂላልን አሸንፎ ብቸኛ ክብሩን ማሳካት ችሏል።

ለ53ኛ ጊዜ (በ53ኛ ዓመቱ) በሚደረገዉ የ2017ቱ የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ አል አህሊ ከአራት ዓመታት በኋላ፣ ለዘጠነኛ ጊዜ ባለ ድል ለመሆን፣ ዋይዳድ ደግሞ ከ6 ዓመታት በኋላ፣ ለሁለተኛ ጊዜ የዋንጫዉ ባለቤት ለመሆን ለፍፃሜዉ በቅተዋል።

የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን 26 ክለቦች ከፍ ማድረግ ችለዋል።

ትልቁ አል አህሊ በግማሽ ፍፃሜዉ የቱኒዝያዉን ኢቶይል ደ ሳህልን ጥሎ ነዉ ለፍፃሜ የበቃዉ። በመጀመርያዉ ጨዋታ ቱኒዝ ላይ 2 ለ 1 ተሸንፎ ቢመለስም፣ አሌክሳንድርያ ላይ ባደረገዉ ጨዋታ 6 ለ 2 በሆነ ሰፊ ዉጤት በማሸነፍ በ7 ለ 4 ድምር ዉጤት ለፍፃሜዉ በቅቷል። ተጋጣሚዉ የሞሮኮዉ ዋይዳድ ካዛ ብላንካ ደግሞ፣ ከአልጀርያዉ ዩኤስኤም አልጀር ጋር በግማሽ ፍፃሜዉ ያደረገዉን ጨዋታ፣ አልጀርያ ላይ 0 ለ 0 ተለያይቶ ሞሮኮ ላይ 3 ለ 1 በማሸነፍ ነዉ በደርሶ መልስ በሚደረገዉ የፍፃሜ ፍልሚያ መብቃት የቻለዉ።

የመጀመርያዉ ጨዋታ ቅዳሜ፣ 18/ 2010 ዓ/ም በግብፅ የሚደረግ ሲሆን፣ በሳምንቱ ሞሮኮ ላይ ይደረጋል።

የዋይዳዱ ሞሃመድ ኦናጄም ግብፅ ላይ በሚደረገዉ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርባቸዉ መዉጣት ቀዳሚ አላማቸዉ እንደሆነ መግለፁን አህራም ኦንላይን አስነብቧል።

ከግብፁ ክለብ በኩል የጉዳት ዜናዊች እየተሰሙ ሲሆን፣ ሆሳም አሾርና ሳሌህ ጎማ ከቅዳሜዉ ጨዋታ ዉጭ መሆናቸዉ ተገልጿል።

ይህንን ጨዋታ ኢትዮጵያዊዉ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ወዬሳ በመሃል ዳኝነት እንደሚመራዉም ታዉቋል።

ግርማይ መረሳ

ግርማይ መረሳ

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ግርማይ መረሳ ነኝ።
ግርማይ መረሳ