በእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ 10ኛዉ ሳምንት መርሃ ግብር ማንቸስተር ዩናይትድ ትልቁን ጨዋታ በድል ተወጥቷል። ማንቸስተር ሲቲ በአሸናፊነቱ ሲቀጥል፣ ቸልሲ ከሜዳዉ ዉጭ፣ ሊቨርፑልና አርሰናል በሜዳቸዉ ድል ቀንቷቸዋል።

ሰባት ጨዋታዎች በተደረጉበት የዕለተ ቅዳሜ መርሃ ግብር፣ ምሳ ሰዓት ላይ ቶተንሃምን ኦልትራፎርድ ላይ ያስተናገደዉ ማንቸስተር ዩናይትድ በአንቶኒ ማርሻል ብቸኛ ጎል አሸንፎ ወጥቷል።

ራሽፎርድን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባዉ ማርሻል በ81ኛዉ ደቂቃ ጎሏን ማስቆጠር ችሏል። ዉጤቱም ሁለተኝነቱን እንዲያስጠብቅ ረድቶታል።

አምስት ጨዋታዎች በተደረጉበት 11፡00 ሰዓት ታላላቆቹ ማንቸስተር ሲቲ፣ አርሰናልና ሊቨርፑል ተጋጣሚዎቻቸዉን መርታት ችለዋል።

ዌስትብሮምን የገጠመዉ ማንቸስተር ሲቲ 3 ለ 2 በመርታት ያለ መሸነፍ ጉዞዉን ቀጥሏል። ሳኔ በ10ኛዉ ደቂቃ ሲቲን መሪ ሲያደረግ፣ ጄይ ሮድሪጌዝ ዌስትብሮምን አቻ ያደረገ ጎል 13ኛዉ ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ ነበር። ነገር ግን ፈርናንዲንሆ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ 15ኛዉ ደቂቃ ላይ ዳግም መምራት የቻሉበትን ጎል አስቆጥሯል።

ራሂም ስተርሊንግ 64ኛዉ ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ መሪነታቸዉ በሁለት ከፍ ቢያደርገዉም፣ ማት ፊሊፕስ 92ኛዉ ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ ጨዋታዉ 3 ለ 2 በማንቸስተር ሲቲ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ማንቸስተር ሲቲዎች ከ10 ጨዋታዎች ዘጠኙን በማሸነፍ፣ በአንዱ ብቻ አቻ ተለያይተዉ ጥሩ አጀማመር አድርገዋል። በአጠቃላይ፣ 17 ጨዋታዎችን አሸንፈዉ፣ በ4ት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዉ፣ 21 ጨዋታዎችን ባለመሸነፍ እየተጓዙ ሲሆን ይህም በታሪካቸዉ ረጅም ርቀት የተጓዙበት ነዉ። ነገር ግን ይህ ቁጥር በቀጣዮቹ ሳምንታት የሚሻሻል ይመስላል።

አርሰናል በሜዳዉ ባደረገዉ ጨዋታ ከመመራት ተነስቶ ስዋንሲ ሲቲን 2 ለ 1 መርታት ችሏል። ሳም ክሉካስ 23ኛዉ ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥሮ ስዋንሲዎች የመጀመርያዉን አጋማሽ በመሪነት ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

አርሰናሎች በሁለተኛዉ አጋማሽ በፍፁም የማጥቃት ኃይል ተጫዉተዉ ያሸነፉባቸዉን ሁለት ጎሎች አስቆጥረዋል። በክረምቱ ክለቡን የተቀላቀለዉ ኮላሲናች 51ኛዉ ደቁቃ ላይ፣ እንዲሁም ራምሴ 58ኛዉ ደቂቃ ላይ ጎሎቹን በስማቸዉ አስመዝግበዋል።

ራምሴ ያስቆጠራት ጎል በክለቡ 50ኛ ጎሉ ስትሆን በዉድድር ዓመቱም ሦስተኛዉ ሆና ተመዝግባለች።

ሊቨርፑል በአንፊልድ ሃደርስፊልድን አስተግዶ 3 ለ 0 መርታት ችሏል። ባለፈዉ ሳምንት ማንቸስተር ዩናይትድን አሸንፎ የነበረዉ ሃደርስፊልድ አንፊልድ ላይም ያልተጠበቀ ዉጤት ሊያስመዘግብ ይችላል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ባለሜዳዎቹ ሊቨርፑሎች አሸናፊ ሆነዋል።

ዳንኤል ስቱሪጅ 50ኛዉ ደቂቃ ላይ የመጀመርያዉን ጎል ሲያስቆጥር፣ ሮበርቶ ፊርሚንሆ ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ፣ 58ኛዉ ደቂቃ ላይ ሁለተኛዉን የጎል ኳስ መረብ ላይ አሳርፏል። የጨዋታዉን የመጨረሻ ጎል፣ ጆርጂንዮ ዊይናልደም 75ኛዉ ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።

ክርስትያል ፓላስ በሜዳዉ ባደረገዉ ጨዋታ በዌስትሃም ዩናይትድ 2 ለ 0 ሲመራ ቢቆይም ከእረፍት መልስ 2 ጎል በማስቆጠር 1 ነጥብ ይዞ ወጥቷል።

ሃቪየር ሄርናንዴዝ በ31ኛዉ ደቂቃ፣ አንድሬ አየዉ 43ኛዉ ደቂቃ ላይ አስቆጥረዉ በመጀመርያዉ አጋማሽ መምራት ቢችሉም፣ ከእረፍት መልስ ሉካ ሚሊቮጄቪች 50ኛዉ ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት፣ እንዲሁም መደበኛዉ የጨዋታ ጊዜ ተፈፅሞ የተጨመረዉ ስድስት ደቂቃ ሲጠናቀቅ 96ኛዉ ደቂቃ ከስድስት ሰከንድ ላይ የአቻነቷን ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ይቺ የዛሃ ጎል በዉድድር ዓመቱ ከተመዘገቡ ዘግይተዉ ከተቆጠሩ ጎሎች መካከል ሁለተኛዋ ሆናለች። ከዚህ ቀደም ራሂም ስተርሊንግ ከዚች ጎል በ28 ሰከንድ የዘገየች ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል። ዛሃ ከጉዳት ተመልሶ ቡድኑን ማገልገል ከጀመረ ወዲህ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ሁለቱም ቡድኑ እስካሁን ላስመዘገባቸዉ አራት ነጥቦች የላቀ አስተዋፅኦ አላቸዉ።

ዋትፎርድ በሜዳዉ ከስቶክ ሲቲ ጋር ያደረገዉን ጨዋታ 1 ለ 0 ተሸንፏል። የቀድሞዉ የማንቸስተር ዩናይትድና የዌስትብሮም ተጫዋች ዳረን ፍሌቸር 16ኛዉ ደቂቃ ላይ የጨዋታዉን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል።

ምሽት 1፡30 ላይ የተደረገዉ የበርንማዉዝና የቸልሲ ጨዋታ በቸልሲ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ኤዲን ሃዛርድ 51ኛዉ ደቂቃ ላይ የአሸናፊነቷን ጎል ማስቆጠር ችሏል።

መጠነኛ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸዉ ቸልሲዎች አራተኛ ደርጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል። ሻምፒዮኖቹ በሚቀጥለዉ ሳምንት ስታምፎርድ ብሪጅ ላይ ማንቸስተር ዩናይትድን ይገጥማሉ።

ግርማይ መረሳ

ግርማይ መረሳ

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ግርማይ መረሳ ነኝ።
ግርማይ መረሳ