የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድና የኤቨርተን ተጫዋች እንግሊዛዊዉ ፊል ኔቭል ኤቨርተንን የማሰልጠን ፍላጎት እንዳለዉ ተገለፀ።

የመርሲሳይዱ ክለብ ባሳለፍነዉ እሁድ በገዛ ሜዳዉ በአርሰናል 5 ለ 2 ከተረታ በኋላ ሆላንዳዊዉን ሮናልድ ኲይማንን ማሰናበቱ ይታወሳል።

የሆላንዳዊዉን መሰናበት ተከትሎ ፊል ኔቭል የኤቨርተንን የአሰልጣኝነት መንበር መረከብ ይፈልጋል። ኔቭል በስፔኑ ቫሌንሲያ በምክትል አሰልጣኝነት የሠራ ቢሆንም በስንብት ክለቡን ለቋል። የ40 ዓመቱ ኔቭል በ2005 ማንቸስተር ዩናይትድን ለቆ ኤቨርተንን ከተቀላቀለ በኋላ በ8 ዓመት ቆይታዉ 303 ጨዋታዎችን አድርጓል።

ኤቨርተኖች በክለባቸዉ ከ23 ዓመት በታች እያሰለጠነ የሚገኘዉን ዴቪድ አንስዎርዝ በጊዚያዊነት እንዲያሰለጥን የሚፈልጉ ሲሆን፣ ረቡዕ በካራባኦ ካፕ ከቸልሲ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ሥራዉን ይጀምራል።

ኤቨርተንን ለማሰልጠን የበርካታ አሰልጣኞች ስም እየተነሳ ሲሆን የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ ኮከብ ሪያን ጊግስም ኤቨርተንን ማሰልጠን እንደሚፈልግ መግለፁ አይዘነጋም።

ሮናልድ ኲይማን ከ16 ወራት ቆይታ በኋላ ከኤቨርተን ተሰናብቷል። ኤቨርተኖች በዘንድሮዉ የዉድድር ዓመት ካደረጓቸዉ ዘጠኝ የፕርሚየር ሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት ሁለቱን ብቻ ነዉ።

ግርማይ መረሳ

ግርማይ መረሳ

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ግርማይ መረሳ ነኝ።
ግርማይ መረሳ