የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዉ ሁለቱም በአቻ ዉጤት ተጠናቀዋል።

ከ140 ሚልዮን በላይ በማዉጣት ቡድናቸዉን ያጠናከሩት ኤቨርተኖች ዛሬም ብራይተንን ገጥመዉ ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። 82ኛዉ ደቂቃ ላይ አንቶኒ ኖካርት ባስቆጠረባቸዉ ጎል በአዲስ መጪዎቹ ብራይተኖች ሲመሩ ቆይተዉ 90ኛዉ ደቂቃ ላይ በተገኘ ፍፁም ቅጣት ምት ከመሸነፍ ድነዋል። ዋይኒ ሩኒ የተገኘችዉን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ጎልነት ለዉጧታል።

ካወጣዉ ገንዘብ አንፃር፣ እንዲሁም ባለፈዉ ዓመት ካስመዘገበዉ ዉጤት አንፃር የተሻለ ግምት ተሰጥቶት የነበረዉ ኤቨርተን እስካሁን ካደረጋቸዉ ስምንት ጨዋታዎች ያስምዘገበዉ ድል ሁለት ብቻ ነዉ። በስምንት ነጥብ 8 የግብ ዕዳ ተሽክሞ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አዲስ መጪዉ ብራይተንም ተመሳሳይ 8 ነጥብ ይዞ ከኤቨርተን በአራት የግብ ክፍያ ተሽሎ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሴንት ሜሪ ላይ የተደረገዉ የሳዉዛምፕተንና የኒዉካስትል ጨዋታ 2 ለ 2 በሆነ ዉጤት ተደምድሟል። አይዛክ ሃይደን በ20ኛዉ ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ኒዉካስትል መምራት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ማኑሎ ጋቢያዲኒ 49ኛዉ ደቂቃ ላይ አስደናቂ ጎል በማስቆጠር ሳዉዛምፕተንን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር። ነገር ግን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አዮዜ ፔሬዝ ኒዉካስትል በድጋሚ መምራት የቻለበትን ጎል ማስቆጠር ሲችል ፍሎሪያን ሌዬዉን ሎንግ ላይ በሠራዉ ጥፋት የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ማኑሎ ጋቢያድኒ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን በድጋሚ አቻ ማድረግ ችሏል።

የዛሬዉን የአቻ ዉጤት ተከትሎ ኒዉካስትል በ11 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ሳዉዛምፕተን ብ9 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ግርማይ መረሳ

ግርማይ መረሳ

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ግርማይ መረሳ ነኝ።
ግርማይ መረሳ