12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ሁለተኛው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌትሪክ መካከል ተከናወነ፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ፈጣን እና የተቆራረጠ የኳስ እንቅስቃሴ ተስተውሏል፡፡

ወደ ጎል በመድረስ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በተለይ 2ኛው እና 19ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳኑሚ ከበረኛ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያመከነውን ኳስ የሚያስቆጭ ነበር፡፡

ተመሳሳይ በሆነ እንቅስቃሴ የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ 58ኛው ደቂቃ በኢትዮጵያ ቡናዎች ኤልያስን ማሞ አውጥተው ኒታንቢን ካስገቡ በኀላ የተሻለ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡

74ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳኑሚ በመስመር በኩል ይዞት ጎል ክልል ውስጥ የገባውን ኳስ አመቻችቶ ለመስዑድ መሐመድ ሲያቀብለው ነፃ ሆኖ የተቀበለው መስዑድ ኳሱን ከመረብ አገናኝቶታል፡፡

ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን የጨዋታው ኮከብ መስዑድ መሐመድ ሆኖ ተመርጧል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለመውሰድ እሁድ ይገናኛሉ፡፡

ጨዋታው ተጠናቆ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ግርማ በቀለ እና መስዑድ ኳስ ላይ ተገናኝተው ግርማ በቀለ መስዑድን ወደጠብ ሊገፋፋ በሚችል መልኩ ሲገፈትረው መስዑድ ዞር ብሎ እንኳን አላየውም፡፡ ይህን የግርማ በቀለ ድርጊት በቅርበት ሲመለከት የነበረው የኢትዮጵያ ቡናው ታዳጊው አቡበከር ናስር እየሮጠ መጥቶ ግርማን ሊያናግረው ሲመጣ መስዑድ አቡበከርን በስሜት ወዳልተገባ ድርጊት እንዳይገባ ሲመልሰው ተመልክተናል፡፡ መስዑድ መሐመድ ግን ያሳየው የታጋሽነት እና ጨዋነት ባህሪ በተለይም እግር ኳስ በብቃት አሳምኖ ማሸነፍ እንጂ በጊዜያዊ ስሜት ተገፋፍቶ ያልተገባ ባህሪ ማሳየት እንደማይገባ በተግባር ያሳየ በመሆኑ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡

 

ግርማይ መረሳ

ግርማይ መረሳ

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ግርማይ መረሳ ነኝ።
ግርማይ መረሳ