በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚዘጋጀው 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር የምድብ ለ ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከአዳማ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከመከላከያ አገናኝቷል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዳማ ከተማን ሲያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።
ከቀኑ 9:20 ላይ የጀመረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የታየበትና በብዙ የጎል ሙከራዎች የታጀበ ነበር።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ኤሌክትሪክ ተጭኖ የተጫወተ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ አዳማዎችም የተሻለ መነቃቃት አይተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ በ61ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ ኤልክትሪኩ ተስፋዬ መላኩ በአዳማው በረከት ደስታ ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። የቁጥር ብልጫቸውን ይጠቀማሉ ተብለው የተገመቱት አዳማዎችም ይባስ ብሎ ተቀይሮ የገባው በላይ አባይነህ በ71ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥሮ ኤሌክትሪክን ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።
በጨዋታውም የአዳማ ከተማው ሱራፌል ዳኛቸው የጨዋታው ኮከብ ሆኗል።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የነበረው ተጠባቂው የቅዱስ ጊዮርጊስና የመከላከያ ከተማ ጨዋታ ያለምንም ጎል ተጠናቋል።
በጥሩ የጨዋታ ፍሰት በማራኪ እንቅስቃሴዎች የታጀበው የሁለቱም ቡድኖች ጨዋታ የተሻለ የጎል ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታውን መሃል ሜዳ ላይ ጨርሰውት ወጥተዋል።
የዕለቱ የጨዋታው ኮከብም የቅዱስ ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም ዞኮ ተመርጧል።

የከተማው ዋንጫ ረቡዕ የምድብ ሀ ጨዋታዎች ቀጥለው ይውላሉ።

ሞገሴ ሽፈራው

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ሞገሴ ሽፈራው ነኝ። ከፎቶው ጎን ያለውን የፌስቡክ ምልክት ተጭነው ሊያገኙኝ ይችላሉ።