በእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር በአንፊልድ የተደረገዉ የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ የጎል ድርቅ ሲመታዉ ኢቲሃድ ላይ ዘጠኝ ጎሎች ተቆጥረዋል። ወደ ሰልኸርስት ፓርክና ቪካሬጅ ሮድ ያመሩት የለንደኖቹ ቸልሲና አርሰናል ደግሞ በተመሳሳይ ዉጤት ተሸንፈዋል።

በአንፊልድ የተደረገዉ የሊቨርፑልና የማንቸስተር ዩናይትድ ጨዋታ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ ሆዜ ሞዉሪንሆ በድጋሚ የመከላከል አጨዋወትን መርጠዉ ከአንፊልድ በአንድ ነጥብ ተመልሰዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜዉን በሊቨርፑል ተበለጠዉ የዋሉት ማንቸስተሮች አንድ ኢላማዉን የጠበቀ የጎል ሙከራ ብቻ አድርገዋል። በአንፃሩ ሊቨርፑሎች ካደረጓቸዉ 19 ሙከራዎች መካከል 5ቱ ኢላማቸዉን የጠበቁ ነበሩ። ነገር ግን የጨዋታዉ ኮከብ ዳቪድ ደሂያ ማንቸስተር ዩናይትዶችን እንደተለመደዉ ታድጓቸዉ ወጥቷል።

ማንቸስተር ዩናይትዶች በዉድድር ዓመቱ ጎል ያላስመዘገቡበት የመጀመርያ የሊግ ጨዋታቸዉ ሲሆን፣ ሊቨርፑሎች 62 በ 38 በሆነ የኳስ ብልጫ ጨዋታዉን ተቆጣጥረዉ ወጥተዋል።

11፡00 ላይ አምስት ያህል ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ማንቸስተር ሲቲ እንደተለመደዉ በጎል ተነበሽብሾ፣ቸልሲ በክርስትያል ፓላስ ያልተጠበቀ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዶ ወጥቷል።

አስደናቂዉ ቤልጅየማዊ ኬቪን ደብሩይነ ሦስት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ባቀበለበት በዚህ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ በሜዳዉ 7 ለ 2 በሆነ ሰፊ ዉጤት ስቶክ ሲቲን ደቁሶታል።

ስድስት ያህል ተጫዋቾች በሰባቱ ጎሎች ላይ ተሳትፈዋል። በመጀመርያዉ አጋማሽ 3 ለ 1 በሆነ ዉጤት ወደ መልበሻ ክፍል ሲገቡ፣ ጋብርኤል ሄሱስ በ17ኛዉ፣ ስተርሊንግ በ19ኛዉና ዳቪድ ሲልቫ በ27ኛዉ ደቂቃ ማንቸስተር ሲቲ 3 ለ 0 የመራበትን ጎሎች አስቆጥረዋል። 44ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ማሜ ቢራ ዲዮፍ የስቶክን ጎል አስቆጥሯል።

ከእረፍት መልስ 47ኛዉ ደቂቃ ላይ ካይል ዎከር በራሱ ላይ ያስቆጠራት ጎል ስቶኮችን ያነቃቃች ብትመስልም ማንቸስተር ሲቲዎች በ7 ደቂቃ ዉስጥ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር የጎል መጠኑን የበለጠ አስፍተዉታል። ስተርሊንግ 55ኛዉ ደቂቃ ላይ፣ ፈርናንዲንሆ 60ኛዉ ደቂቃ ላይ፣ እንዲሁም ሌሮይ ሳኔ 62ኛዉ ደቂቃ ላይ ካስቆጠሩ በኋላ፣ በርናርዶ ሲልቫ 79ኛዉ ደቂቃ ላይ የመደምደሚያዋን ጎል አስቆጥሯል።

ማንቸስተር ሲቲዎች 79 በ 21 በሆነ ልዩነት ጨዋታዉን የተቆጣጠሩት ሲሆን በ8 ጨዋታዎች 29 ጎሎችን በማስቆጠር ከ1894-95 ወዲህ የመጀመርያዉ ክለብ ሆኗል። በወቅቱ ይህንን ማድረግ ችለዉ የነበሩት ኤቨርተኖች ናቸዉ።

በሌላ ጨዋታ፣ ወደ ሰልኸርስት ፓርክ ያቀናዉ ቸልሲ ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናግዶ ተመልሷል። ሰባት ጨዋታ አድርገዉ ምንም ነጥብና ምንም ጎል ያልነበራቸዉ ክርስትያል ፓላሶች የመጀመርያ ጎላቸዉንም ሆነ የመጀመርያ ነጥባቸዉን በአምናዉ ሻምፒዮን ቸልሲ ላይ ማስመዝገብ ችለዋል። 11ኛዉ ደቂቃ ላይ አዝፕልኩዌታ ወደራሱ መረብ ባሳረፋት ጎል መምራት የቻሉት ባለሜዳዎቹ ፓላሶች፣ ከ7 ደቂቃዎች በኋላ ባካዮኮ ጎል አስቆጥሮ አቻ ቢሆኑም፣ ከጉዳት የተመለሰዉ ዊልፍሬድ ዛሃ 45ኛዉ ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ ድል ማድረግ ችለዋል።

ቶተንሃም ሆትስፐር በሜዳዉ በርንማዉዝን አስተናግዶ በክርስትያን ኤሪክሰን የ47ኛ ደቂቃ ጎል 1 ለ 0 በሆነ ዉጤት መርታት ችሏል።

በሌሎች ጨዋታዎች፣ በርንሌይ ከዌስትሃም 1 ለ 1 ሲለያዩ፣ አንዲ ካሮል በሁለት ቢጫ ካርድ ገና በጊዜ በ27ኛዉ ደቂቃ ከሜዳ ተወግዷል። ጎሎቹን አንቶኒዮ በ19ኛዉ ደቂቃ ለዌስትሃም ሲያስቆጥር፣ ዉድ በ85ኛዉ ደቂቃ የአቻነቷን ጎል ማስቆጠር ችሏል። ስዋንሲ ሲቲ ሃደርስፊልድን 2 ለ 0 አሸንፎ በወጣበት ጨዋታ ሁለቱንም ጎሎች ታሚ አብርሃም በ42ኛዉና በ48ኛዉ ደቂቃዎች ላይ አስቆጥሯል።

ምሽት ላይ የተደረገዉ የተደረገዉ የዋትፎርድና የአርሰናል ጨዋታ በዋትፎርድ 2 ለ 1 አሸፊነት ተጠናቋል። 39ኛዉ ደቂቃ ላይ መርትሳከር ባስቆጠራት ጎል ሲመሩ የነበሩት አርሰናሎች መሪነታቸዉን ማስጠበቅ ተስኗቸዉ ድል ሆነዋል። ቤለሪን በሰራዉ ጥፋት የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ዲኔይ አስቆጥሮ አቻ መሆን የቻሉት ዋትፎርዶች፣ በጭማሪ ሰዓት 92ኛዉ ደቂቃ ላይ ቶም ክሌቨርሊ ባስቆጠራት ጎል አሸንፈዉ ወጥተዋል።

ሊጉን ማንቸስተር ሲቲ በ22 ነጥብና በ25 ንፁህ ጎል ሲመራዉ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ በ20 ነጥብና በ19 ንፁህ ጎል ሁለተኛ ነዉ። ቶተንሃም በ17 ነጥብና በ10 ንፁህ ጎል ሦስተኛ፣ ዋትፎርድ በ15 ነጥብ ያለ ምንም ጎል አራተኛ ሲሆን፣ ቸልሲ፣ አርሰናል፣ በርንሌይና ሊቨርፑል በእኩል 13 ነጥብ በጎል ተበላልጠዉ ተከታዮቹን ደረጃዎች ተከታትለዉ ይዘዋል።

ግርማይ መረሳ

ግርማይ መረሳ

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ግርማይ መረሳ ነኝ።
ግርማይ መረሳ