ሜሲ አርጀንቲናን ከፍ ሲያደርግ ሳንቼዝ አንገቱን ሰበረ

በደቡብ አሜሪካ ዞን (ኮንሜቦል) አርጀንቲና በሜሲ ሃትሪክ የዓለም ዋንጫዉን የቀጥታ ተሳትፎ ስታሳካ አሌክሲስ ሳንቼዝና ቺሊ የዓለም ዋንጫዉን በቤታቸዉ ሆነዉ ለመከታተል ተገደዋል።

ማክሰኞ ሌሊቱን በተደረገዉ የደቡብ አሜሪካ የማጣርያ ጨዋታ ኢኳዶርን ከሜዳዋ ዉጭ የገጠመችዉ አርጀንቲና ባለ ድንቅ ግራ እግሩ ልጇ ባስቆጠራቸዉ ሦስት ጎሎች ታግዛ ዓለም ዋንጫዉን ተቀላቅላለች።

ጨዋታዉ በተጀመረ ገና በመጀመርያዉ ደቂቃ ኢኳዶራዉያን በኢባራ አማካይነት ጎል አስቆጥረዉ የአርጀንቲናዉያንን የዓለም ዋንጫ ጉዞ ለማጨለም ጀምረዉ የነበረ ቢሆንም፣ ሊዮኔል ሜሲ ከእረፍት በፊት በ12ኛዉና በ20ኛዉ ደቂቃ እንዲሁም ከእረፍት መልስ በ62ኛዉ ደቂቃ ላይ ያስቆጠራቸዉ ሦስት ጎሎች የሩስያዉን የዓለም ዋንጫ የሚካፈሉበት የቀጥታ የተሳትፎ ደረጃን ማግኘት ችለዋል። ድሉን ተከትሎ አርጀንቲና በ28 ነጥብ ከጨዋታዉ በፊት የነበረችበትን የ6ኛ ደረጃን በማሻሻል ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በሌላ የሌሊቱ ተጠባቂ ጨዋታ፣ ማጣርያዉን በበላይነት አስቀድማ ያጠናቀቀችዉ ብራዚል በሜዳዋ ያስተናገደቻት ቺሊን 3 ለ 0 በመረምረም ከዓለም ዋንጫ ዉጭ አድርጋታለች።

ከጨዋታዉ በፊት ቺሊያዉያን በ26 ነጥብና በ2 የጎል ክፍያ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የነበሩ ሲሆን የሦስተኛነት ደረጃዉን ለአርጀንቲናዉያን አስርክበዉ፣ የአርጀንቲናን ቦታ ተረክበዉ የማጣርያ ጨዋታቸዉን ፈፅመዋል።

ቺሊዎች ፓዉሊንሆ ጎል ካስቆጠረባቸዉ በኋላ ቢያንስ የፕለይ ኦፍ ደረጃዉን ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። የሲቲዉ አጥቂ በክለብ አጋሩ ላይ አከታትሎ ያስቆጠራቸዉ ጎሎች የቺሊን ተስፋ ሙሉ በሙሉ ያጨለሙ ሆነዋል።

የብራዚልን የማሸነፊያ ጎሎች ፓዉሊንሆ በ55ኛዉ፣ ጋብርኤል ሄሱስ በ57ኛዉና በ90ኛዉ ደቂቃዎች ላይ ማስቆጠር ችለዋል።

በዚህ ዞን የቀጥታ ተሳትፎን የማግኘት ዕድል የነበራት ሌላዋ ሃገር ፔሩ በሜዳዋ ከኮሎምቢያ ጋር ያደረገችዉን ጨዋታ በአቻ ዉጤት በመፈፀሟ የፕለይ ኦፍ ደረጃዉን ይዛ ለማጠናቀቅ ተገዳለች።

በጨዋታዉ 56ኛዉ ደቂቃ ላይ የሪያል ማድሪድ ንብረት የሆነዉ የባየር ሙኒኩ አጥቂ ሃሜስ ሮድርጌዝ ጎል አስቆጥሮ እየተመሩ የነበረ ቢሆንም ከ20 ደቂቃዎች በኋላ ፓዉሎ ጉሬሮ የአቻነት ጎል በማስቆጠር ወደ ፕለይ ኦፍ ደረጃ እንዲመጡ አስችሏቸዋል።

ፔሩ በሜዳዋ ያገኘችዉ አንድ ነጥብ ለፕለይ ኦፍ እንድትበቃ ያስቻላት ቺሊ ወደ ብራዚል ሄዳ ያስመዘገበችዉ የ3 ለ 0 ሽንፈትና፣ ሌላዋ ባለ ተስፋ ፓራጉዋይ በዞኑ የመጨረሻ ደርጃ ላይ በምትገኘዉ ቬኒዚዌላ በሜዳዋ 1 ለ 0 መሸነፏ ነዉ። ፓራጉዋይ ያንጌል ሄሬራ 84ኛዉ ደቂቃ ላይ ባስቆጠረዉ ብቸኛ ጎል ተሸንፋ በ24 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃቸዉ ላይ ረግተዉ ማጣርያዉን አጠናቀዋል።

ፔሩ ከ1 ንፁህ ጎል ጋር በ26 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን፣ በፕለይ ኦፍ ኒዉዚላንድን ትገጥማለች።

ይህንን ዞን በሁለተኝነት ያጠቀቀችዉ ኡራጋይ ከቦሊቪያ ጋር ያደረገችዉን ጨዋታ ስድስት ጎል አስቆጥራ 4 ለ 2 በሆነ ዉጤት መርታት ችላለች። ስድስቱንም ጎሎች አጥቂዎቿና ተከላካዮቿ አስቆጥረዉታል። ጋስቶን ሲልቫ በ24ኛዉ ደቂቃ በራሱ መረብ ላይ ባሳረፈዉ ጎል ቦሊቪያዎች መምራት የጀመሩ ሲሆን፣ ሌላዉ ተከላካይ ማርቲን ካሲሬስ 39ኛዉ ደቂቃ ላይ የአቻነት ጎል ማስቆጠር ችሏል። ካቫኒ 42ኛዉ ደቂቃ ላይ፣ ሉዊስ ሱዋሬዝ 60ና 76ዉ ደቂቃ ላይ አስቆጥረዉ መሪነታቸዉን ወደ 4 ለ 1 ከፍ ሲያደርጉት፣ አንጋፋዉ ተከላካይ ዲየጎ ጎደን 79 ኛዉ ደቂቃ ላይ በራሱ መረብ ላይ ለቦሊቪያዎች ሁለተኛ የሆነች ጎል አስመዝግቦላቸዋል።

በዚህም መሠረት፣ ኡራጋይ በ31 ነጥብ ብራዚልን ተከትላ ሩስያ የምትደርስበትን ደረጃ ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች።

የደቡብ አሜሪካ ዞን (ኮንሜቦል) የ2018 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ደረጃ

ሃገር                       ነጥብ                   ጎል

1.ብራዚል                 41                      30

2. ኡራጋይ                31                      12

3. አርጀንቲና             28                       3

4. ኮለምቢያ            27                        2

5. ፔሩ                     26                       1

6. ቺሊ                     26                       -1

7. ፓራጉዋይ            24                       -6

8. ኢኳዶር                20                       -3

9. ቦሊቪያ                14                       -22

10. ቬኒዚዌላ           12                       -16

ግርማይ መረሳ

ግርማይ መረሳ

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ግርማይ መረሳ ነኝ።
ግርማይ መረሳ