በጉጉት ሲጠበቅ የነበረዉና በስታንፎርብሪጅ ስታዲዬም ጠንካራ ፉክክር ያስተናገደዉ የቼልሲና አርሰናል ጨዋታ ያለምንም ጎል 0-0 በሆነ አቻ ዉጤት ፍፃሜዉን አግኝቷል፡፡ ከ2011ዱ የ5-3 ድል በኃላ ስታንፎርብሪጅ ላይ ባለፉት 6 አመታት ማሸነፍ ያልቻሉት የሰሜን ለንደኖቹ አርሰናል ከሜዳቸዉ ዉጭ እንደመጫወታቸዉ መጠን ወሳኝ 1 ነጥብ አስመዝግበዉ ተመልሰዋል፡፡

በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረዉ ብራዚላዊዉ የቼልሲ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ዴቪድ ሊዉዝ በሰራዉ ያልተገባ አጨዋወት ምክንያት በእለቱ አልቪትር ማይክል ኦሊቨር አማካኝነት በ87ኛዉ ደቂቃ ከሜዳ በቀጥታ ቀይ ካርድ ተሰናብቷል፡፡

የምዕራብ ለንደኑ ቼልሲ በጣሊያናዊዉ አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ስር ስታንፎብሪጅ ስታዲዬም ላይ ከ27 ጨዋታዎች በኃላ ያለግብ ያጠናቀቀበት የመጀመሪያው ጨዋታ ሁኖ ተመዝግቧል፡፡

ሌላዉ ተጠባቂ ጨዋታ ኦልድትራፎርድ ላይ የተደረገዉና እንግሊዛዊዉ አጥቂ ዋይኒ ሮኒ ከ13 አመታት በኃላ ወደ እናት ክለቡ ተመልሶ የቀድሞ ክለቡን በተቃራኒው
የገጠመበት የማንችስተር ዩናይትድና ኢቨርተን ጨዋታ በዩናይትዶች ፍፁም የበላይነት ተጠናቋል፡፡ የጆዜ ሞሪንሆዉ ቡድን ገና በ4ኛዉ ደቂቃ በኢኳዶራዊዉ የቀድሞው የዊጋን አትሌቲክ የመስመር ተጫዋች አንቶኒዮ ቫሌንሻ ከኒማኒያ ማቲች የተሻገረለትን ኳስ በሚገባ ተጠቅሞ ቀያይ ሰይጣኖችን ገና በጊዜ የጎል አካዉንታቸዉን እንዲከፍቱ አድርጓቸዋል፡፡

ከዚች ጎል መቆጠር በኃላ እስከ 83ኛዉ ደቂቃ ድረስ በሁለቱ ቡድኖች መካከል በርካታ ያለቀላቸዉ ኳሶችን ቢያገኙም ኳስና መረብን ግን ማገናኘት ተስኗቸዉ አምሽቷል፡፡ መደበኛዉ የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ 7 ደቂቃዎች ሲቀሩ በአርመናዊዉ ሄነሪክ ሚክሂታሪያን አማካኝነት ቀያይ ሰይጣኖቹ 2ኛ ጎላቸዉን ሲያስቆጥሩ 89ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ሮሜሉ ሉካኩ በቀድሞ ቡድኑ ላይ ጎል በማስቆጠር የተለዬ የደስታ አገላለፅ አሳይቷል፡፡

90+2 ተቀይሮ የገባው አንቶኒዮ ማርሻል በፍፁም ቅጣት ምት ተጨማሪ ጎል በመጨመር ጨዋታው በዩናይትድ የ4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ዉጤቱን ተከትሎም የአንድ ከተማ ክለብ የሆኑት ሲቲና ዩናይትድ በተመሳሳይ 13 ነጥብና 14 የጎል ብዛት ሊጉን መምራታቸዉን ከወዲሁ ተያይዘዉታል፡፡