በ6ኛዉ ሳምንት የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ መርሃ ግብር የመጀመረያ ቀን ዉሎ ስምንት ጨዋታዎች ተደርገዋል።

በ8፡30 ዌስትሃም ዩናይትድን የገጠመዉ ቶተንሃም ሆትስፐር ለ20ደቂቃዎች ያህል በ10 ተጫዋች ለመጫወት ቢገደድም ወደ ጎል ማግባቱ መንገድ በተመለሰዉ ሃሪ ኬን ሁለት ጎሎችና በክርስትያን ኤሪክሰን አንድ ጎል ታግዞ ባለ ሜዳዉን ዌስትሃምን 3 ለ 2 በሆነ ዉጤት ድል ማድረግ ችሏል። በክረምቱ የዝዉዉር መስኮት ከፒኤስጂ ቶተንሃምን የተቀላቀለዉ ሰርጂ አዉሬር በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ በተወገደበት ጨዋታ ዌስትሃሞች በቺቻሪቶና በኩያቴ አማካይነት ሁለት ጎሎችን አስቆጥረዉ ነጥብ ለማግኘት ትግል ማድረግ ችለዉ ነበር።

11፡00 ላይ ስድስት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ሁለቱ የማንቸስተር ከተማ ክለቦች በማሸነፍ አንገት ላንገት እንደተናነቁ ቀጥለዋል። በአምስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ተስኖት አሰልጣኝ የቀየረዉን ክርስትያል ፓላስን ያስተናገዱት ማንቸስተር ሲቲዎች በሳኔ፣ በስተርሊንግ፣ በአጌዌሮና በዴልፍ አማካይነት አምስት ጎሎችን አስቆጥረዉ በጎል ሲንበሸበሹ፣ የከተማ ተቀናቃኛቸዉ ማንቸስተር ዩናይትድ በሉካኩ ብቸኛ ጎል አሸንፎ ወጥቷል።

አጀማመሩ ያላማረዉ አልቫሮ ሞራታ ሃትሪክ በሠራበት ጨዋታ ቸልሲዎች 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ዉጤት ስቶክ ሲቲን መርታት ችለዋል። የቸልሲዎችን ተጨማሪ ጎል ስፔናዊዉ ፔድሮ አስቆጥሯል።

በሌሎች የ11 ሰዓት ጨዋታዎች፣ በጉዲሰን ፓርክ በርንማዉዝን የገጠሙት ኤቨርተኖች ከመመራት ተነስተዉ 2 ለ 1 ሲረቱ፣ ወደ ዌልስ ያቀናዉ የማርኮ ሲልቫዉ ዋትፎርድ በተመሳሳይ 2 ለ 1 በሆነ ዉጤት አሸንፏል። በርንሌይ ከሃደርስፊልድ ደግሞ ያለ ግብ ጨዋታቸዉን በአቻ ዉጤት ፈፅመዋል።

ምሽት 1፡30 ላይ የተደረገዉ የሌይስተር ሲቲና የሊቨርፑል ጨዋታ በሊቨርፑል 3 ለ 2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ዌስትሃም 2 – 3 ቶተንሃም
ሄርናንዴዝ (65′)፣                 ኬን (34’፣38′)፣
ኩያቴ (87′)                         ኤሪክሰን (60′)

በርንሌይ 0 – 0 ሃደርስፊልድ

ኤቨርተን 2 – 1 በርንማዉዝ
ኒያሴ (77’፣82′)                  ኪንግ (49′)

ማንቸስተር ሲቲ 5 – 0 ክርስትያል ፓላስ
ሳኔ (44′)፣ ስተርሊንግ (51’፣59′)፣

አጉዌሮ (79′)፣ ዴልፍ (89′)

ሳዉዛምፕተን 0 – 1 ማንቸስተር ዩናይትድ
ሉካኩ (20′)

ስቶክ 0 – 4 ቸልሲ
ሞራታ (2’፣77’፣82′)፣

ፔድሮ (30′)

ስዋንሲ 1 – 2 ዋትፎርድ
አብርሃም (56′)                         ግሬይ (13′)፣
ሪቻርሊሰን (90′)

ሌይስተር ሲቲ 2 – 3 ሊቨርፑል
ኦካዛኪ (45′ + 3)                          ሳላህ (15′)፣

ቫርዲ (69′)                                   ኩቲንሆ (23′)፣
ሄንደርሰን (68′)

ግርማይ መረሳ

ግርማይ መረሳ

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ግርማይ መረሳ ነኝ።
ግርማይ መረሳ