ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ነሐሴ 04/2017 ባወጣው የምርመራ ዘገባ

ከስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ጋር በተያያዘ በአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ በወጣው የተከለከሉ መድኃኒቶችና ዘዴዎች ዝርዝር ውስጥ በቀዳሚነት የተካተተውና EPO ወይም በሳይንሳዊ ስያሜው Erythropoietin የተባለው መድኃኒት ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው የግሸን ፋርማሲ ያለምንም የሐኪም ትዕዛዝ በቀላሉ እንደሚሸጥና ስፖርተኞችም በቀላሉ እየገዙ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ መግለፁ ይታወሳል፡፡

 

ስለሆነም ምንም እንኳን ጋዜጣው የአገራችንን ስፖርት በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ካለው የዶፒንግ ችግር ለመከላልና በተለይም በአትሌቲክሱ ቀደም ሲል ጀምሮ በአለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የተገነባውን መልካም ገፅታ ለማስቀጠል በየደረጃው እየተካሄደ ያለውን ዘርፈ-ብዙ ጥረት በሚዛኑ ያላስቀመጠ፤ አንድን ፋርማሲ ብቻ በናሙናነት በመውሰድ ኢትዮጵያ ውስጥ የዶፒንግ ምርቶችን በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል የሚያሳይ እና ስፖርተኞችም እየገዙ ይጠቀማሉ የሚል መደምደሚያ ያለው ፅሁፍ ማውጣቱ ትክክል ባይሆንም በምርመራ ዘገባው ላይ የቀረቡትን መረጃዎች መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት እና በፌዴራል እና በአዲስ አበባ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣናት ኢንቨስቲጌሽን በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በዚህም መድኃኒቱ በጋዜጣው ላይ በተጠቀሰው የግሸን ፋርማሲ ውስጥ እንደሚገኝ በፍተሻ ማረጋገጥ እንዲሁም የዘጋርዲያን ጋዜጠኞች በላኩት ደረሰኝ መሰረት መድኃኒቱን ከፋርማሲው መግዛታቸውን ማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጋዜጣው ላይ ፎቶግራፋቸው የታተሙ መድኃኒቶችን መለያ ቁጥር በመመርመር ፋርማሲው በደረሰኝ ያስገባቸውን መድኃኒቶች ያለሐኪም ትዕዛዝ መሸጡ ተረጋግጠዋል፡፡

በዚህም መሰረት ፋርማሲው ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ስታዲየም የሚገኘው የግሸን ፋርማሲ ለሶስት ተከታታይ ወራት እንዲዘጋና አገልግሎት እንዳይሰጥ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ በተጨማሪም የቅርንጫፍ መድኃኒት ቤት ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ይበልጣል አድማሱ የሙያ ግዴታቸውንና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ በመሆኑ የሙያ ፈቃዳቸው ለስድስት ወራት እንዲታገድና ፈቃዳቸውንም ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንዲመልሱ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡

በአገራችን የወንጀል ህግ አንቀፅ 526 የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በሚመለከት ማንኛውም ሰው በተፈጥሮ እና በስልጠና የተገኘውን የአካል ብቃት በጊዜያዊ መልክ በይበልጥ እንዲጨምር በማድረግ በስፖርት ውድድር ጊዜ አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ የበላይነት ለማግኘት የሚረዱ በህግ የተከለከሉና ጎጂ የሆኑ ሰው ሰራሽ ነገሮችን ያመረተ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ፣ የሸጠ፣ በባለሞያነት ያዘዘ፣ ያከፋፈለ ወይም የተጠቀመ ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀምባቸው ያደረገ እንደጥፋቱ ክብደት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡

 

በዚህ የህግ ድንጋጌ፣ በአለም አቀፉ ደረጃ በተከለከሉ መድኃኒቶች፣ በተዘረጉ የፀረ-ዶፒንግ የአሰራር ስርዓቶች እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ከምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሞያዎችና አመራሮች፣ ከፋርማሲ ባለቤቶችና ባለሞያዎች፣ ከጤና ባለሞያዎች እና ከሌሎችም አካላት ጋር በኢትዮጵያ ሆቴል የጋራ ውይይት ተካሂዷል፡፡

መረጃው የኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር  ነው፡፡