በ40 ሚ.ፓ ዋጋ ከሊጉ ሻምፒዮን ቼልሲ ወደ ዩናይትድ የተቀላቀለዉ ኒማኒያ ማቲች ወደ ቀያይ ሰይጣኖቹ ለመዘዋወር በቀላሉ መወሰን እንደቻለ ተናግሯል፡፡

በአወዛጋቢው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ስርም ለሁለተኛ ጊዜ የሚሰለጥን ሲሆን በሶስት የዉድድር አመትም ሁለት የፕርሚየር ሊግ ዋንጫን ማሳካት ችሏል፡፡

ከዝዉዉሩ በኃላ ለማንችስተር ዩናይትድ ቴሌቪዥን አስተያየቱን የሰጠዉ ማቲች፡ ማንችስተር ዩናይትድ አለማችን ላይ ከሚገኙ ታላላቅ ክለቦች መካከል አንዱ ነዉ፤ የኔ ምኞትም በድጋሜ ከጆዜ ጋር መገናኘት ነበር፡ አሰልጣኙንም ክለቡንም በጣም እወዳቸዋለሁ፡ ለዚህም ነዉ በቀላሉ ዩናይትድን ለመቀላቀል የወሰንኩት ሲል ተናግሯል፡፡

ኒማኒያ ማቲች በመጪው ማክሰኞ በአዉሮፓ ሱፐር ካፕ ከሪያል ማድሪድ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ የመሠለፍ እድል ይኖረዋል፡፡

አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ በመጀመሪያ የዉድድር ዘመን ቆይታቸዉ ዩናይትድን ከሻምፒዮኑ ቼልሲ በ24 ነጥቦች አንሶ በ6ኛ ደረጃ እንዲያጠናቅቅ ቢያደርጉትም በአቋራጭ የኢሮፓ ሊግን በማሸነፍ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፏቸዉን አግኝተዋል፡፡

በሌላ ዜና ቼልሲ የሌሲስተር ሲቲዉን አማካይ ድሪንክ ዋተርን በዝዉዉር ኢላማቸዉ አነጣጥረዉበታል፡፡

እንግሊዛዊዉ የቀበሮዎቹ አማካይ ዳኒ ድሪንክዋተር የኒማኒያ ማቲችን ከቼልሲ መዉጣት ተከትሎ የሰማያዊዎቹ አለቃ አንቶኒዮ ኮንቴ ወደ ስታንፎርብሪጅ ለማስኮብለል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ተጫዋቹ በ2015-16 የዉድድር አመት ሌሲስተር ሲቲ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ለቀበሮዎቺ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ጣሊያናዊዉ አሰልጣኝ የባየርሙኒኩን ሬናቶ ሳንቼዝ የአርሰናሉን አሌክስ ኦክስሌድ ቻምበርሊን የኢቨርተኑን ሮዝ ባርክሌን እና ድሪንክዋተርን የአማካይ ክፍላቸውን ለማጠናከር አንዳቸዉን የማስፈረም ፍላጎት አሳድረዉ በእቅዳቸው አካተዋቸዋል፡፡

ባሳለፍነዉ የዉድድር አመት ከቀበሮዎቹ ጋር የ4 ኮንትራት የፈረመው ተጫዋቹ ወደ ቼልሲ የመዛወሩ ነገር ጠባብ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ክለቡ ሌሲስተር ተጫዋቹን የመሸጥ ፍላጎት አለመኖራቸው እንደምክንያት ቀርቧል፡፡

ሰማያዊዎቹ ተሳክቶላቸው ድሪንክዋተርን የሚያዛዉሩት ከሆነ ከቀድሞው የቡድን አጋሩ ንጎሎ ካንቴ ጋር በድጋሚ የመጫወት እድልን ያገኛል፡፡