የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2009 ዓ/ም ዉድድር በሁለት ምድቦች ተከፍሎ ሲካሄድ ከቆየ በኋላ በጅማ ከተማ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከከፍተኛ ሊጉ፣ በአጠቃላይ ከአንድ እስከ ሦስት ያለዉን ደረጃ የያዙት ቡድኖች በቀጣዩ የዉድድር ዓመት፣ በ2010 ዓ/ም በኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ከ14-16 ያለዉን የመጨረሻዉን ደረጃ በመያዝ የወረዱትን ጅማ አባቡናን፣ ኢትዮ ንግድ ባንክንና አዲስ አበባ ከተማን ተክተዉ ይጫወታሉ። ጅማ አባቡና እና አዲስ አበባ ከተማ በ2008 ዓ/ም በከፍተኛ ሊጉ በአንድ ምድብ ተደልድለዉ ሲጫወቱ ከነበሩ በኋላ፣ አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ነበር በ2009 ዓ/ም በፕርሚየር ሊጉ የተካፈሉት።

በከፍተኛ ሊጉ ሁለቱንም ምድቦች በቀዳሚነት ያጠናቀቁት ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲና ጅማ ከተማ አስቀድመዉ የ2009 ዓ/ም የፕርሚየር ሊጉን ወራጅ ቡድኖች መተካታቸዉ የተረጋገጠ ነበር!

ምድብ “ሀ” በአብዛኛዉ የሁለት ክለቦች፣ በተለይም ወደ መጠናቀቂያዉ አካባቢ የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲና የመቀለ ከተማ ትንቅንቅ ብቻ የታየበት ሲሆን፣ ወልዋሎ አ.ዩ.፣ መቀለ ከተማን በ3 ነጥብ በመብለጥ በ64 ነጥብ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል።

በአንፃሩ፣ ምድብ “ለ” እስከ መጨረሻዉ ሳምንት ጨዋታ በአራት ቡድኖች መካከል የማለፍ ፍጥጫ ተስተዉሎበታል። ጅማ ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ወልቂጤ ከተማና ሀላባ ከተማ በቅደም ተከተል 53 ( ጅማ ከተማና ሀዲያ ሆሳዕና በጎል ተበላልጠዉ )፣ 52 እና 51 ነጥብ በመያዝ በእኩል የማለፍ ዕድል፣ የመጨረሻዉን ሳምንት ጨዋታ አድርገዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ የዚህን ምድብ የመጨረሻ ጨዋታ አስደናቂና እንዲጠበቅ አድርጎት የነበረዉ ጉዳይ፣ ከላይ ያሉት አራቱ ቡድኖች እርስ በርስ የተገናኙበት ጨዋታ በመሆኑ ነበር!

በእርግጥ፣ በምድብ “ሀ” ወልዋሎ አ.ዩ. እና መቀለ ከተማ በመጨረሻዉ ሳምንት እርስ በርስ ተገናኝተዉ ነበር። ነገር ግን ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረዉ መቀለ ከተማ ወልዋሎ አ.ዩን በልጦ አንደኛ ለመሆን ከ7 ጎል በላይ በሆነ በሆነ ልዩነት ማሸነፍ ነበረበት። ነገር ግን ጨዋታዉ 1 ለ 1 በሆነ ዉጤት ነበር የተጠናቀቀዉ።

በምድብ “ለ” በተደረጉት የመጨረሻዉ ሳምንት ጨዋታዎች ጅማ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 3 ለ 1 በማሸነፍ በአንደኝነት ምድቡን ማጠናቀቅ ችሏል። ሀዲያ ሆሳዕና ከሀላባ ከተማ 0 ለ 0 በመለያየታቸዉ ምክንያት ሀዲያ ሆሳዕና ምድቡን በሁለተኝነት በመፈፀም ወደ ፕርሚየር ሊጉ ሦስተኛ ሆኖ ለማለፍ ከመቀለ ከተማ ጋር ለሚደረገዉ ጨዋታ ማለፍ ችሎ ነበር።

መቀለ ከተማና ሀዲያ ሆሳዕና፣ ወልዋሎ አ.ዩን እና ጅማ ከተማን ተከትለዉ በ2010 የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ማክሰኞ ከሰዓት፣ በድሬዳዋ ከተማ እርስ በርስ ባደረጉት ጨዋታ መቀለ ከተማ 2 ለ 1 በማሸነፍ በ2010 ዓ/ም የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል።

በመጨረሻም፣ አጠቃላይ የከፍተኛ ሊግ አሸናፊዉን ለመለየት በተደረገዉ የማጠቃለያ ጨዋታ፣ አቅሌሲያ ግርማ በራሱ ላይ በተሠራ ጥፋት የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ጅማ ከተማን አሸናፊ ማድረግ ችሏል። በዚህም፣ የየምድቡ መሪዎች ጅማ ከተማና ወልዋሎ አ.ዩ. የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆኑ፣ ጅማ ከተማ አጠቃላይ አሸፊ በመሆኑ የወርቅ ሜዳሊያ፣ ወልዋሎ አ.ዩ. የብር ሜዳሊያ፣ እንዲሁም መቀለ ከተማ የነሃስ ሜዳልያቸዉን ያጠለቁበት የዉድድር ዓመት ሆኖ አልፏል።

መጪዉ ዓመት፣ የ2010 ዓ/ም የዉድድር ዘመንስ እነማንን ከፕርሚየር ሊጉ አዉርዶ እንማንን ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕርሚየር ሊጉ ያሳድጋል? የዛ ሰዉ ይበለን!!!

ግርማይ መረሳ

ግርማይ መረሳ

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ግርማይ መረሳ ነኝ።
ግርማይ መረሳ