በታላቅ ትንቅንቅ ለበርካታ ወራት ሲካሄድ የነበረው የከፍተኛ ሊግ እግር ኳስ ውድድር ከሳምንት በፊት መጠናቀቁ ይታወቃል::
በሁለት ምድቦች ተከፍሎ ሲካሄድ የነበረው ይህ ውድድር በምድብ ‘ሀ’ በወልዋሎ አዲግራት በምድብ ‘ለ’ በጅማ ከተማ አንደኝነት እንዲሁም በመቀሌ ከተማ እና በሃድያ ሆሳዕና ሁለተኛነት መጠናቀቁን ተከትሎ ወልዋሎን እና ጅማ ከተማን ተከትሎ በሶስተኛነት ወደ ፕሪሜርሊጉ ለመቀላቀል የሚደረገው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ዛሬ በድሬደዋ ከተማ ስታድየም መቀሌ ከተማ ሃድያ ሆሳዕናን 2 ለ 1 በማሸነፍ የፕሪሜርሊግ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል።
ከዕለቱ 10:00 ላይ የጀመረው ይህ ፍጥጫ ጨዋታው በተጀመረ 3ኛው ደቂቃ ላይ ሃድያዎች ጎላ ቢያስቆጥሩም ተጨዋቹ ከጨዋታ ውጭ በመሆኑ ጎሉ ተሽሯል።
የዕለቱ ጨዋታ እንደተጀመረ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ የዕለቱ የመሃል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ስምንተኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ሊያቋርጡት ተገደዋል።
የዝናቡን ማባራት ተከትሎ በድጋሚ የተጀመረው ጨዋታ በ14ኛው ደቂቃ እንዳለ ደባልቄ የመጀመሪያውን ጎል በማስቆጠር ሃድያን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር።
የዚህ ጎል ደስታ ግን ከሁለት ደቂቃዎች በላይ ሊሆን አልቻለም።
በዚህ አመት ድንቅ ብቃቱን በማሳዬት ለመቀሌ ከተማ ወሳኝ የሆኑ ጎሎችን ሲያስቆጥር የነበረው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከርቀት አክርሮ በመምታት በ16ኛው ደቂቃ ክለቡ መቀሌን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከረፍት መልስ በሁለቱም ወገን የማለፍ ተስፋ በመሰነቅ ቢንቀሳቀሱም ጨዋታው ሊጠናቀቀ 12 ደቂቃ ሲቀረው መቀሌዎች ጎል አካባቢ ያገኙትን የቅጣት ምት ዮሴፍ ታዬ ወደ ጎል በመቀየር መቀሌ ከተማ ሃድያ ሆሳዕናን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ፕሪሜር ሊጉ እንዲቀላቀል አድርጓል።
ይህንን ተከትሎም መቀሌ ከተማ የትራንስ ኢትዮጵያን ከፕሪሜር ሊጉ መውደቅ ተከትሎ ለአመታት ወካይ ያልነበረውን የትግራይ ክልል ወልዋሎ አዲግራትን ተከትሎ ሁለተኛ የክልሉ ተወካይ መሆን ችሏል።
ሃድያ ሆሳዕናም ከአመት በፊት በዘጠኝ ነጥብ ከፕሪሜር ሊጉ መውጣቱ ይታወሳል።

በመጨረሻም ወልዋሎ አዲግራት ፣ ጅማ ከተማ እና መቀሌ ከተማ ወደ ፕሪሜር ሊጉ የተቀላቀሉ ሶስቱ ክለቦች ሆነዋል።

ሞገሴ ሽፈራው

ይሄን ፅሁፍ ያቀረብኩላችሁ ሞገሴ ሽፈራው ነኝ። ከፎቶው ጎን ያለውን የፌስቡክ ምልክት ተጭነው ሊያገኙኝ ይችላሉ።