ለስፖርት መስፋፋት ከሚያስፈልጉ በርካታ ግብአቶች ዋነኞቹ የውድድሮች መኖር እና ማዘውተሪያ ስፍራዎች መሟላት እንዲሁም የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ተቋማት መበራከት ናቸው፡፡ በቀበሌ በድርጅቶች እና በየትምህርት ቤቱ ይደረጉ የነበሩ ውድድሮች መቀዛቀዝ ለስፖርቱ መዳከም ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ግንባር ቀደሞች ናቸው፡፡

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በስሩ በሚገኙ  ኩባንያዎች እና ተጋባዥ በሆኑ ድርጅቶች በየዓመቱ የሚያደርገውን የእግር ኳስ ውድድር መክፈቻ የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም እንደተለመደው በመቻሬ ሜዳ አካሂዶ ነበር፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም በቦታው ተገኝተው የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጡ በተጠየቅው መሰረት ከበርካታ የሚዲያ ተቋማት ጋር በቦታው ታድመናል፡፡ 

የመክፈቻ ውድድሩ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር  ዶክተር አረጋ ይርዳው ከጋዜጠኞች የሰራተኞች ውድድር አስመልክቶ እዲሁም አጋጣሚውን በመጠቀም ከዛም ወጣ ያሉ እና ድርጅቶቻቸውን የሚመለከት ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ነበር፡፡

ዶክተር አረጋ ይርዳውን ያስደሰታቸው አስደናቂና ፈጣን መልስ የሰጡበት ጥያቄ የቀረበላቸው ከዝግጅት ክፍላችን (ከኢትዮጵያንስፖርት ዶት ኮም ethiopiansport.com) የቀረበው ጥያቄ ሲሆን ‹‹ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ለ14 ዓመታት ሰራተኛውንና ቤተሰቡን የሚያቀራርብ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮችን በሰራተኞች መካከል የሚያደርግ ሲሆን እንዲሁም የተለያዩ ተጋባዥ ኩባንያዎችን ከማሳተፉ በተጨማሪ በሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ ባለቤትነት ከሚንቀሳቀሱት እህት ኩባንያዎች ውጪ ኢትዮ ቴሌኮም (ደቡብ ምእራብ ቀጠና) በተጋባዥነት መካፈል ጀምሯል፡፡ ይህ ውድድር በየዓመቱ ሲደረግ የሰራተኛው ልጆች እና ቤተሰቦች በቦታው ተገኝተው ውድድሩን ተመልከተው ተዝናንተው እና ቤተሰባዊ ቅርርብ ፈጥረው እንደሚለያዩ ይታወቃል፡፡ የልጆች ቡድን በመመስረት ከሰራተኛው ጎን ለጎን ውድድር ቢደረግ ከታዳጊዎቹ መሃከል በዚህ ዕድል ተጠቅመው ሀገርን እስከመጥቀም የሚደርሱ ልጆች ሊፈጠሩ ይችላሉና ይሄን ጉዳይ አስባችሁበታልን?››  የሚል ነበር፡፡

‹‹ቆንጆ ሀሳብ ነው፡፡ አልከፍልህም ግን ሀሳቧን እወስዳታለሁ፡፡ አይዲያው ቆንጆ ነው›› በማለት ከመለሱ በኋላ በፕሮግራሙ ማብቂያ ላይ አብረዋቸው ያሉ የማኔጅመንት አባላትን ‹‹ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ  እንዲሆን›› ሲሉ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡ በዚህም መሰረት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በዓመታዊው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የስፖርት ውድድር ላይ የታዳጊዎች ውድድር ሊጀመር እንደሚችል አረጋግጠዋል፡፡

 

 

ከኢትዮጵያን ሰፖርት ዶትኮም በተጨማሪ በስፍራው የተገኙት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች ዶክተር አረጋ የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

     

ጥያቄ፦ የዘንድሮ ውድድር ከሌላው ጊዜ ውድድሮች ምን የተለየ ነገር አለው?

ዶክተር አረጋ፡- እውነቱን ለመናገር ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡ የተለየ ነገር ያደረገው እንደሚታውቀው የዛሬ ሁለት ወር ወልዲያ ስታዲየምን አስመርቀናል፡፡ ያ ስሜታችን (sprite)  እስካሁን እንዳለ ነው፡፡ ስለዚህ እሱ ቆንጆ ነው፡፡ ለዚህም ነው ይሄንን ስንጨርስ መጨረሻውን  በዓል ወልዲያ ሄደን እናከብራለን ያልኩት፡፡ ከአምናው ዘንድሮ  ፖዘቲቭ የሆነ ነገር አለን፡፡ አካሄዳችን ጥሩ ይመስላል፡፡

ጥያቄ፡- ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሶስት ሚለዮን ብር የቦንድ ግዢ ፈጽማችኋል ሲባል ሰምተናል ……?

 ዶ/ር አረጋ፡- እሱን ላስተካክለው፡፡ እኛ ያደረግነው 25 ኩባንያዎች አሉ፡፡ ቦንድ ለመግዛት ኩባንያዎች ራሳቸው እንደ ግለሰብ ይገዛሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ኩባንያዎች 25ቱ የሶስት ሚሊዮን ብር ቦንድ እንዲገዙ እናደርጋለን፡፡ እሱን ምክንያት አድርገን ደግሞ ሰራተኛውን እንቀሰቅሳለን፡፡ ከዛ በኋላ ጠቅለል አድርገን እርዳታ ለማድረግ እንሞክራለን፡፡

ጥያቄ፡- እንደዚህ አይነት ውድድሮች በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ላይ ቢደረጉም ሌሎች ድርጅቶች ላይ ብዙም አልተለመደም ምክንያቱ ምን ይመስለዎታል?

ዶ/ር አረጋ፡- እናንተ (ጋዜጠኞችን ለማለት ነው) በደንብ አድርጋችሁ አስተዋውቁ፣ ቀስቅሱዋ፡፡ ሌሎቹንም ኑ ብላችሁ ጠይቁ፡፡ እኛ ስታዲየም አለን እድሜ ለሼክ መሐመድ ይሄን የመሰለ ስታዲየም አለን፡፡ ሼክ መሐመድ 74 ኩባንያዎች አሏቸው ቅድም እንደተናገርኩት የምንፈልገው ሁሉም አንድ ላይ ሆኖ እንዲገናኙ ብናደርግ ጥሩ ይሆናል፡፡ ሁለተኛ ድሮ ድሮ እኔ በእናንተ ዕድሜ በነበርኩበት ጊዜ ሁሉም የየራሱ ቡድን ነበረው፡፡ አየር መንገድ የራሱ ቲም ነበረው፣ ኮተን የሚባል ቡድን ነበር፣ ሲሚንቶ የሚባል ቡድን ነበር፡፡ አሁን ወደዛ  መሄድ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ ተጫዋቾች የሚፈልቁት አንድም ትምህርት ቤት ውስጥ ነው አንድም ድርጅቶች ውስጥ ነው፡፡ ያን ከማድረግ አኳያ ጥሩ ነው፡፡ የእኛ ዋናው አላማችን ተጫዋቾች አፍልቀን ኢንተርናሽናል ወይም ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች መፍጠር ሳይሆን ስፖርቱ ለጤንነት፣ ለማኔጅመንት፣ ለመገናኘት፣ ለፍቅር፣ ፕሮዳክቲቪቲ ለመሆን ያግዘናል ብለን ስለምናስብ ማኔጅመንቱ እና ሁሉም ሰራተኛ አብሮ በሚሆንበት ጊዜ ትልቅ ፍቅር ይፈጥራል ብለን ስለምናምን ነው ውድድር የምናዘጋጀው፡፡

ለምሳሌ የወልዲያው ጉዞአችን 700 የሚሆኑ ሰራተኞቻችን በስሊፒን ባግ ነው ያደርነው ለ3 ቀን፡፡ ይሄ አይነት ነገር ለአገራችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ አለቃም ጭፍራም እኩል ነው የተኙት፡፡ ለእንደዚህ አይነት መቀራረብና ወዳጅነት ለመፍጠር ስፖርት ትልቅ መሣሪያ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የአቅም ጉዳይ፣ የጊዜ ጉዳይ ይቸግር ይሆናል፡፡ አሁን ግን በሚዲያው የማየው ስፖርት አካባቢ የሚታየው የሰው ፍላጎትም የሌላውን ውድድር (የውጪውን) ከመከተል አኳያ አንዳንድ ቴሌቭዥኖች ላይ እንደሚያሳዩት ከመጠን በላይ ተከታይ ወጣት የበዛበት አገር መሆኑን ነው፡፡ ስፖርት ከመስራት አኳያ ለወጣቱ ደግሞ ከስፖርት  የተሻለ ምን ነገር አለ?

 

ጥያቄ፡- ልምዳችሁን ለሌሎች ከማካፈል አኳያ ወደናንተ እንዲመጡ ምን ሰርታችኋል?

ዶ/ር አረጋ፡- ግብዣ አድርገናል ለምሳሌ ኢትዮቴሌኮም (ደቡብ ምዕራብ ቀጠና) ጎረቤታችን ስለሆነ በየዓመቱ ይጫወታል፡፡ የምንሰጠውን ሽልማትም ያሸንፋል ይወስዳልም፡፡ ስፖርት ለማንም ሰው ክፍት መሆን ያለበት እንጂ ገደብ አያስፈልገውም፡፡ እንዴት እናፍልቀው? ወጣቱ ቴሌቭዥን በማየት ብቻ ስፖርተኛ መሆን አይቻለም፡፡ ስለዚህ የወጪ መጋራት ጉዳይ የእያንዳንዱ ድርጅት ድርሻ ነው፡፡ ኩባንያዎች እኮ ሀብታም ናቸው፡፡ ስፖርት ደግሞ የሚጠይቀው በጣም ትንሽ ነው፡፡ በስፖርቱ አማካኝነት ደግሞ የሚገኘው ፍቅር እና ሥራ ከመጠን በላይ ቆንጆ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ሙሉ በሙሉ ወጪውን እንችላለን ከሰራተኛ የምንወስደው የለም፡፡ ሌሎቹ ምናልባት ሎጂስቲክሱ አልተመቻላቸው ይሆናል፡፡ ስፖርት ኳስ ጨዋታ ብቻ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ድርጅት ቼዝም ሆነ ሌላ መጫወት ይችላል ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ አሁን ያለን ፈተና ትልልቅ ፓርኮች ቢኖሩ ፓርክ ትሄዳለህ፣ ገና ነን ብዙ ቲያትር ቤቶች ተስፋፍተው ቢሆን ኖሮ ትሄዳለህ፡፡ ቴሌቭዥን ባይኖሮ ሰው የሚዝናናበት ነገር የለም፡፡ ኩባንያዎች ሁሉም የራሳቸው የሆነ ትንሽ ነገር ማድረግ ቢችሉ ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወደ እንጦጦ ቢሄድ ወጣቱ ሜዳ ፍለጋ ጨዋታ መጫወት ፈልጎ ከእንጨት ላይ ሲታገል ታያለህ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን መርዳት ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ኳስ የሚጫወቱ አካውንታንት ቢኖሩ ልንቀጥር እንችላለን፡፡ ፕሮፌሽናል ስራቸውን እየሰሩ የእረፍት ጊዜያቸውን ስፖርቱን እንዲያሳድጉበት እንፈልጋለን፡፡

 

በዘንድሮው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በሚያዘጋጀው ዓመታዊ የሰራተኞች ስፖርት ውድድር ተሳታፊ ቡድኖች 11 ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል የቴክኖሎጂ ግሩፑ 25 ድርጅቶች አራት ቡድን መስርተው ይሳተፋሉ፡፡ እነሱም ቴክ ሳር ቤት፤ ቴክ አቃቂ፤ ቴክ መገናኛ እና ቴክ ሳሚት ናቸው፡፡

ከተጋባዥ ኩባንያዎችና ተቋማት መካከል ደግሞ ፖልሪየስ፤ ዳሽን ባንክ፤ ኢትዮቴሌኮም ደቡብ ምዕራብ ቀጠና፤ ናሽናል ሞተርስ፤ ሞሐ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ( ንፋስ ስልክ ፋብሪካ)፤ አዲስ ኢንተርናሽናል ኬተሪንግ፤ ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ፤ ሆራይዘን አዲስ ጎማ፤ ኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ፤ ኢትዮ ሌዘር ኢንዱስትሪ እና ሜፖ ኮንትራክቲንግ እና ማናጅመንት ሰረቪስ ናቸው፡፡

በመክፈቻው በተካሄደ የእግር ኳስ ጨዋታ ቴክ መገናኛ ከቴክ አቃቂ ተጫውተው ቴክ መገናኛ 3 ለ 2 አሸንፏል፡፡ ውድድሩ ለሶስት ወራት ሲካሄድ ይቆያል፡፡